Sunday, 19 May 2013

ማን ነው ወንጀለኛው?


በከፍተኛ ደረጃ የህዝብ እምነት ያጣው የካንጋሮው ፍርድቤት ምንም አይነት የህግ ወይም የሞራል የበላይነት ሳይኖረው፤ የህሊና እስረኞቹን የእድሜ ልክና እና ሌሎች ቅጣቶችን እንዴት ሊሰጥ ይችላል? ማነው ፈራጁ? ማንስ ነው ተፈራጁ? ማን ነው ጥፋተኛው። ህግን ያዋረደ? ወይስ ስለነጻነት፣ ስለ ዲሞክራሲ አቤት ያለ?
በፍትህ እና በፍትህ ፈላጊዎች ላይ እየቀለደ እና ተቋሙን እያዋረደ የሚገኘው ወያኔ ዛሬም እንደትላንቱ ሌላ የበደል ጩኸት ከተባዳዮቹ ለበዳዮቹ እንዳይሰማ በጉጅሌ “ዳኞ” ተብየዎች አማካኝነት ውሳኔ ሰጥቷል። እውነተኛ ፍትህ ሀገራችን ውስጥ ጠፍቶ መቀበሩን ለማሳየት ሲል ባስቀመጣቸው የፍትህ ተወናያን ዳኞች አማካኝነት አረፍን እንቀመጥ ዘንድ ፍትህን ትመኙታላችሁ እንጅ አታገኙትም ሲል መልክቱን በአሻንጉሊቶች ፍርድቤቶች አማካኝነት አስተላልፏል።
የገዥው ፓርቲ ጉዳይ አስፈፃሚ ዳኞች ሰሞኑን የሰጡት ፓለቲካዊ ውሳኔ የአገልጋይነታቸውን ታማኝነት ማረጋገጫ እንጅ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ህወሃት እያለ ፍትህና ፍትህ ፈላጊዎችን ማገናኘት የማይታሰብ መሆኑን በድጋሜ ተረጋግጧል፡፡ ፍትህ የነፃነትና የእኩልነት ማረጋገጫ፤ ግለሰቦችና ቡድኖች በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረጊያ እና የአንድ ማኅበረሰብ የሞራል እሴቶች ተፈፃሚነት ማሳያ ነበር፡፡ ፍትህ በሌለበት ነፃነት፣ እኩልነት፣ ሰላም፣ ልማት እና ዲሞክራሲ ትርጉም የላቸውም፡፡
ለዚህም ነው ራሱ የፍትህ ስርአቱ ተቋም የካድሬዎች እስረኛ ነው የምንለው። ተቋማት ነጻ አልወጡም፣ ህዝባችን በጎጠኝነት የአገዛዝ አባዜ ይሰቀያል። በማንነቱ ይሰደዳል፣ ይታሰራል። ታዲያ ማን ነው ጥፋተኛው? በዳዩ ወይስ ተበዳዩ?
ዜጎች በሀገራቸው የመኖር፣ የመናገር ፍትህ የማግኘት ተስፋቸው እንደገና ተቀብሯል። ተዋርደናል፤ ውርደት እስከ መቼ? ኢትዮጵያዊ እምቢተኝነታችን፣ ክብርና ኩራታችን፣ ታሪካችን በወያኔዎች ተደፍሯል። በፋሲካ የጀግናው ሰማእታት የአቡነ ጴጥሮስ የመታሰቢያ ሀውልት ለረጅም ጊዜ ከተቀመጠበት፣ ከመታሰቢያነቱ ስፍራ አሻራነቱ ተነስቷል። በዚሁ ዋዜማ እነ አንዷለምአራጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ ክንፈሚካኤል ደበበ፣ ናትናኤል መኮነን፣ ምትኩ ዳምጤ፣ ዮሃንስ ተረፈ እና ሻምበል የሺዋስ ይሁን አለም ላይ በፋሲካ ዋዜማ አይሁዶች የህሊና እስረኞቹ ይሰቀሉላቸው ዘንድ ፈረዱ።
በፋሲካ በወያኔ ጨለማ ቤት ውስጥ የተዘጉ፣ የተረሱ ዜጎችም አሉ እነ በቀለ፣ ርእዮት፣ ውብሸት እና እነ ጀኒራል ተፈራ ማሞ እና ሌሎቹም። አሁንም በፋሲካ ህዝቡ እየተሰደደ፣ እየተፈናቀለ ነው። በአንጻሩ አይሁዶች እጃቸውን በደም እየታጠቡ ከደሙ ንጹህ ለመሆን ሲሉ ውስኪ ሲራጩ ይታያሉ። ማን ነው ወንጀለኛው?
ኢህአዴግ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በሾማቸው “ዳኞች” ተብየዎች ስም እያፈራረሳት ነው። ትውልድን የቁም እስረኛና አንገቱን እንዲደፋ እንዲሸማቀቅ እያደረጉት ነው። ሀገራችን በወረበሎች አንገቷን ደፍታ የወያኔዎች መሳለቂያ ሆናለች። እናድናት።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፡ የበደል ትልቅና ትንሽ የለውም። በወያኔ ያልተገረፈ፣ ያልተሰደደ፣ ያልተገደለ፣ ያልታሰረ፣ ያልቆሰለ፣ ሀብት ንብረቱን ያልተወረሰ፣ ያልተዋረደ፣ አንገቱን ያልደፋ፣ ያልተበደለ፣ ፍትህን ያልተነፈገ፣ የእምነት ነጻነቱን ያልተገፈፈ ዜጋ የለም። ያጣነው ብዙ ነው። ያጣነውን የማስመለስ ኢትዮጵያዊ ግዴታ አለብን። ሀገራችን ኢትዮጵያ ይህን ውርደትና መከራ እና አይን ያወጣ ጭካኔ ዘረኝነት ብዝቶና ተባብሶ ህልውናዋ ከመጥፋቱ ዜጎቿ የህሊና እስረኞች ሁነው ፍትህ አጥተው ከማለቃቸው በፊት የሚደርሱላት ጀግኖችን ትሻለች።
ወጣቱ ትውልድ ከገባበት የፍርሃት አረንቋ ወጥቶ፣ ፍርሃቱን በጀግነነቱ በጥሶ ኢትዮጵያንና ወገኑን ለማዳንና ነጻነትን በመሰዋእቱ ከፍሎ ለሀገራችን ብርሃን የመሆኛ ጊዜው አሁን ነው። እምቢ ብለህ የነጻነት ተስፋ የሆኑ ህዝባዊ ሃይሎችን ተቀላቀል። ትግል በአንድ ጀምበር የሚያልቅ አይደለም። በርካታ ረጅምና አስቸጋሪ ፈተናዎች ያሉበት፣ የሚጠበቁበት ነው። ቁም ነገሩ ይህንን የተጋረደብህን ፈተና ተፈትነህ ማለፉ ላይ ነው ጀግንነቱ። እንዲህ አይነት ፈተና አምባገነን መንግስት እሰከ አለ ድረስ ለነጻነት፣ ለዲሞክራሲና ለፍትህ መከበር በሚነሱ ሃይላት ላይ የሚኖርና የሚቀጥል በመሆኑ፤ በወያኔ በሚደርስብን የስቃይ ውርጅብኝ ሳንበረከክ ለፍትህ ስርአት መከበር ለህግ የበላይነት መስፈን ለሀገር አንድነት የምናደርገውን ትግል በማጠናከር መቀጠልና ግንባር ቀደም ታጋዮች መሆን ይኖርብናል።
ግንቦት 7 የፍትህ የዲሞክራሲና የነጻነት ንቅናቄ ለፍትህ መቆም ሲል ነፃነቱንና ሀገሩን የሚወድ ዜጋ ሁሉ በማናቸውም መንገድ ወያኔን የመታገል ሞራላዊ ግዴታ አለበት ይላል፡፡ ከትግሉ ባሻገር በነጻነት ታጋዮች ላይ የሀሰት ምስክር የሚሰጡትን፣ ፍትህን የሚየዛቡ ዳኞችና አቃቤዓነ-ህግን የክህደት ሥራዎቻቸውን መዝግቦ መያዝ፣ በዓይነ ቁራኛ መከታተል የሁላችንም ግዴታ ነው፡፡
ህዝብ በሃሰት ምስክሮች፣ ዳኞችና አቃቢያነ-ህግ ላይ ቁጣውን የሚገልጽበት ጊዜ ተቃርቧል፡፡ በወያኔ ወኔ ቢስ አድርባዮች ፍትህ ስትቀበር፣ ዘረኝነት ሲወደስ፣ ታጋዮቻችን ሲገደሉ፣ ሲንገላቱና ሲበደሉ ሲታሰሩ ማየት በቃን ብለናል፡፡ ፍትህን የሚያረክሱትን የወያኔ ቅጠረኞችን በቁርጠኛነት፣ አምርረን እንታገላለን፡፡ የወያኔ ቡችላ ፍርድቤት አገልጋዮች ወዮላችሁ! ያላገጣችሁበት ፍትህ እናንተን ባልጠበቃችሁት ሁኔታ፣ ግዜና ቦታ ትጠየቃችኋለች፡፡ ስለዚህ ራሳችሁን ከቁም እስረኝነትና አገልጋይነት፣ አሽከርነትና ከአደርባይነት ታወጡ ዘንድ ጊዜው አልረፈደባችሁም። እድሉን የመጠቀም ሃላፊነት የእናንተ ነው። እኛ ግን በቃ ብለናል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
G7 Editor
May 10,2013

No comments:

Post a Comment