Sunday, 2 December 2012

ኢሳት ዜና:-የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ጉባኤውን ሲያጠናቅቅ የ77 ዳኞችን ሹመት አጽድቋል።የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ፍቅሩ አያና ከምክር ቤት አባላቱ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ቢቀርብባቸውም፣ ከፍተኛ አመራሮች ስለፈለጉዋቸው ብቻ እንዲሾሙ መደረጉን የኦህዴድ ምንጮች ገልጸዋል።


ከፍተኛ ሙስና ፈጽመዋል የተባሉት ግለሰብ የኦሮምያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ


ኢሳት ዜና:-የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ጉባኤውን ሲያጠናቅቅ የ77 ዳኞችን ሹመት አጽድቋል።የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ፍቅሩ አያና ከምክር ቤት አባላቱ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ቢቀርብባቸውም፣ ከፍተኛ አመራሮች ስለፈለጉዋቸው ብቻ እንዲሾሙ መደረጉን የኦህዴድ ምንጮች ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባላት በአቶ ፍቅሩ ላይ ካቀረቡዋቸው የመቃወሚያ ሀሳቦች መካከል ግለሰቡ በሙስና የተዘፈቁ ናቸው፣ በዞናቸው ዳኛ ሆነው በሰሩበት ወቅት በህዝብ የተጠሉና ህዝብን ያንገላቱ ናቸው፣ የስነምግባር ችግር አለባቸው፣ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም የሚሉት ይገኙበታል። የክልሉ ባለስልጣናት ከምክር ቤት አባላት ለቀረበባቸው ተቃውሞ አጣርተን መልስ እንሰጣለን የሚል ድፍንፍን ያለመልስ በመስጠት ሹመቱ እንዲጸድቅ አድርገዋል።
የምክር ቤት አባላቱ በባለስልጣኑ አሰራር ላይ ነቀፌታ ሲያቀርቡ እንደነበር ታውቋል።
በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳን ጨምሮ የስራ አስፈጻሚዎች የስልጣን ሹም ሽር ይኖራል የሚል አጀንዳ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ አጀንዳው እንዲሰረዝ ተድርጓል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አቶ አለማየሁን ለመተካት ሀሳብ ቢቀርብም በሚተካው ሰው ላይ የስራ አስፈጻሚዎች ለመስማማት ባለመቻላቸው እንዲቀር ተድርጓል። አንዳንድ የስራ አስፈጻሚ  አባላት ስብሰባ ረግጠው እስከመውጣት መድረሳቸውን ለማወቅተ ችሎአል።
በሰሞኑ የምክር ቤት ስብሰባ ላይ አርብ እለት ከተገኙት ከምክትል ፕሬዚዳንቱ ከአቶ አብዱላዚዝ በስተቀር ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በማጠቃለያው ጉባኤ ላይ አልተገኙም።
ሰሞኑን ለአቶ ሙክታር ከድር የተሰጠው የምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትርነት ቦታ በተወሰነ መጠን በምክር ቤቱ ውስጥ ይነሳል ተብሎ የተጠበቀውን ተቃውሞ ማብረዱ ታውቋል።
በሌላ ዜና ደግሞ አዳማ 5ኛውን ከንቲባ ሾማለች። ከሙስና ጋር በተያያዘ ከህዝብ በቀረበ ተቃውሞ ከስልጣን እንዲባረሩ በተደረጉት የተወካዮች ምክር ቤት አባሉ በአቶ ጉታ ላንጮሬ በአቶ ባካር ሻሌ ተተክተዋል። አቶ ባካር ሻሌ አቶ በረከት የሚመሩት የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ምክት ሃላፊ የነበሩ ናቸው።
አንዳንድ ወገኖች ግለሰቡ በእርግጥም ከሙስናና ከአስተዳደር ብቃት ጋር በተያያዘ በከተማው ህዝብ ዘንድ ተቃውሞ ተነስቶባቸው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ከስልጣናን የተባረሩት ግን ምናልባትም በኦህዴድ ውስጥ ከተፈጠረውን ችግር ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።
ኢሳት የከንቲባውንና የከተማ ልማት ቢሮ ሀላፊውን ከስልጣን መባረር መዘገቡ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment